የደመወዝ ማሻሻያው ትርጉም ኖሮት እንዲቀጥልና የሸቀጦች የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር መከላከል የሁሉም ሀላፊነት መሆኑ ተገለፀ።

NWCIV:01-11-2025 15:25pm

ወልድያ፦ ጥቅምት 11/2018 ዓ. ም (ሰሜን ወሎ ኮሙኒኬሽን) የሰሜን ወሎ ዞን ሲቪል ሰርቪስ የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ሃገራዊ የደመወዝ ጭማሬውን አስመልክቶ በወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትውውቅ አካሄደ። የሰሜን ወሎ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ከድር ሙስጠፋ እንደገለፁት የተደረገው የደመወዝ ማሻሻያ የመንግስት ሰራተኛውን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል። ማሻሻያው የአገልግሎት አሰጣጡን በጥራት በውጤታማነትና በቅልጥፍና ያለምንም አድሎ በመፈፀም ለላቀ የህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልም ነው ብለዋል። የደመወዝ ማሻሻያው ትርጉም ኖሮት እንዲቀጥልና የሸቀጦች የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር መከላከል የሁሉም አካል ሀላፊነት መሆኑን አሳስበዋል። የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉ አድሴ እንዳሉት ተቋሙ ለሀገረ መንግስት ግንባታው ውጤታማነት ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል ብለው በመጣንባቸው ጊዜያቶች በየደረጃው ያሉ አመራርና ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች የአገልጋይነት ስሜት ተላብሰው ህዝቡን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፤ አሁንም በማገልገል ላይ ናቸው ብለዋል። ለአመራሩና ለመንግስት ሰራተኛው የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የኑሮ ማሻሻያና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች መልስ ያገኙበት ነው ያሉት ሀላፊዋ ሀገራዊ የደመወዝ ጭማሪውን መሰረት ያደረገባቸው ሀሳቦችና መመሪያዎች ዙሪያ ውይይት በማድረግ ግልፅነት መፍጠር ተችሏል ብለዋል። በየደረጃው ያሉ የሰው ሀይሎች ያለማንም ጎትጓች ሀገራዊ የሪፎርም ትግበራው እውን እንዲሆን ሁሉም የተጣለበትን ሀላፊነት በአግባቡ መወጣት አለበት በማለት ሀላፊዋ አሳስበዋል። የዞኑ ገንዘብ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ጀነቴ አያሌው እንደገለፁት የደመወዝ ጭማሪው ያስፈለገበት ምክንያት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት፣ የስራ ተነሳሽነትን ለመፍጠርና ህገወጥነትን ለመቀነስ ታስቦ መሆኑን ገልፀዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ውይይቱ በወጡ መመሪያዎችና ደንቦች መሰረት ለመስራት የሚያስችል ነው ብለው የደመወዝ ጭማሪውን ተከትሎ የሚደረጉ የሸቀጦችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የዋጋ ጭማሪዎችን ከንግድና ከህግ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ህገወጦችን መከላከል ይገባል ብለዋል።